Psalms 19

እግዚአብሔር የጽድቅ ፀሓይ

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤
የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያውጃሉ።
2ቀን ለሌላው ቀን ይናገራል፤
ሌሊትም ለሌሊት ዕውቀትን ይገልጣል፤
3ንግግር የለም፤ ቃል የለም፤
ድምፃቸው በጆሮ የሚሰማ አይደለም።
ወይም የሚናገሩት የላቸውም፤ ቃላት የለም፤ ከእርሱ ምንም ድምፅ አይሰማም

4ያም ሆኖ ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፣
ቃላቸውም
ሰብዓ ሊቃናት የሩምና ሱርስት እንዲሁ ሲሆኑ፣ ዕብራይስጡ ግን ድንበራቸው ይላል።
እስከ ዓለም ዳርቻ ይወጣል።
እርሱ በሰማያት ለፀሓይ ድንኳን ተክሏል፤
5ፀሓይም ከእልፍኙ እንደሚወጣ ሙሽራ ይወጣል፤
ወደ ግቡም እንደሚሮጥ ብርቱ ሰው ደስ ይለዋል።
6መውጫው ከሰማያት ዳርቻ ነው፤
ዑደቱም እስከ ሌላኛው ዳርቻ ነው፤
ከትኵሳቱም የሚሰወር የለም።

7 የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤
ነፍስንም መልሶ ያለመልማል፤
የእግዚአብሔር ሥርዐት የታመነ ነው፤
አላዋቂውን ጥበበኛ ያደርጋል።
8 የእግዚአብሔር ሕግጋት ትክክል ናቸው፤
ልብን ደስ ያሰኛሉ።
የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፤
ዐይንን ያበራል።
9 እግዚአብሔርን መፍራት ንጹሕ ነው፤
ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
የእግዚአብሔር ፍርድ የታመነ፣
ሁለንተናውም ጻድቅ ነው፤
10ከወርቅ ይልቅ የከበረ፣
እጅግ ከጠራ ወርቅም የተሻለ ነው፤
ከማር ይልቅ ይጣፍጣል፤
ከማር ወለላም ይበልጥ ይጥማል።
11ደግሞም አገልጋይህ በእርሱ ጥንቃቄ ያደርጋል፤
እርሱንም መጠበቅ ወሮታ አለው።

12ስሕተቱን ማን ሊያስተውል ይችላል?
ከተሰወረ በደል አንጻኝ።
13ባሪያህን ከድፍረት ኀጢአት ጠብቅ፤
እንዳይሠለጥንብኝም ርዳኝ፤
ያን ጊዜ ያለ እንከን እሆናለሁ፤
ከታላቅ በደልም እነጻለሁ።

14መጠጊያዬና አዳኜ እግዚአብሔር ሆይ፤
የአፌ ቃልና የልቤ ሐሳብ፣
በፊትህ ያማረ ይሁን።
Copyright information for AmhNASV